Hivtest.no logo

እንኳን ወደ HIVTEST.NO በደህና መጡ

የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግ ከፈለጉ፣ ወደ ጠቅላላ ሐኪምዎ ወይም የምርመራ ክሊኒክ በመሄድ እንዲጀምሩ እንመክራለን። ነገር ግን፣ ይህ ለእርስዎ አማራጭ ካልሆነ፣ SjekkpunktMinuttest ወይም ሌሎች የተለያዩ የምርመራ ክሊኒኮች ውስጥ ስምዎን የማያጋልጥ ፈጣን የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግ ይችላሉ። እነዚህ ቦታዎች ሌሎች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችንም የመመርመር አገልግሎት፣ እንዲሁም እርዳታ እና ምክር ይሰጣሉ።

ከእነዚህ አገልግሎቶች ውስጥ አንዳቸውም ለእርስዎ አማራጭ ካልሆኑ፣ ስምዎ የማይጋለጥበት እና ነፃ የኤች.አይ.ቪ ፈጣን ምርመራን በፖስታ ሊያገኙ ይችላሉ፣ ውጤቱንም በ15 ደቂቃ አካባቢ ውስጥ ያገኛሉ።

በፖስታ ቤት በራስ የሚደረግ የኤች.አይ.ቪ ምርመራን ማን ሊያገኝ ይችላል?

ይህ ውስን በሆነ ደረጃ የኤች.አይ.ቪ ምርመራን ላደረጉ ወይም ፈጽሞ ተመርምረው ለማያቁ ሰዎች እና ለኤች.አይ.ቪ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ለሆኑ ሰዎች ነው።

ለኤች.አይ.ቪ ይበልጥ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ቡድኖች፡-

 • ከወንዶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወንዶች። 
 • ስደተኞች። 
 • ጾታቸውን የለወጡ ሰዎች። 
 • ወሲብን የሚሸጡ ሰዎች።


ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የአንዱ አባል ከሆኑ እና በማንኛውም ምክንያት በምርመራ ማእከል ውስጥ መመርመር ካልቻሉ በዋናው ገጽ ላይ ባለው ቻት ላይ ራስን-መመርመሪያን ለማዘዝ ይበረታታሉ። ማንነትዎ ሳይጋለጥ ከአንዱ ቡድናችን ጋር ቻት ማድረግ እና ከዚያም የራስ መመርመሪያን የማዘዝ እድል ያገኛሉ። ቻት ማድረግ ካልፈለጉ ከእነዚህ ድርጅቶች ለአንዱ መደወል ይችላሉ።

የኤች.አይ.ቪ የራስ ምርመራን እንዴት ማድረግ እችላለው?

የራስ ምርመራው ለኤች.አይ.ቪ ከተጋለጡ ከ6 ሳምንታት በኋላ ትክክለኛ ውጤቶችን ሊሰጥዎት ይችላል፣ ነገር ግን 12 ሳምንታት እስኪያልፍ ድረስ ምርመራው ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ አይደለም። ይህ የሆነበት ምክንያት የፀረ እንግዳ አካላት ምርመራ ስለሆነ እና በበሽታው ከተያዙ ምርመራው ፖዘቲቭ ውጤቶችን ለማሳየት እስከ 12 ሳምንታት ስለሚወስድ ነው።

1.

ከአንዱ ቡድናችን ጋር ቻት በማድረግ መመርመሪያውን እዚህ ማዘዝ ይችላሉ። ቻት ማድረግ ካልፈለጉ ከእነዚህ ድርጅቶች ለአንዱ መደወል ይችላሉ።

2.

ምርመራውን ለማድረግ ከሚያስፈልግዎት ኪት ጋር በፖስታ ቤት በጥንቃቄ የታሸገ ኤንቨሎፕ ይደርስዎታል።

3.

የተጠቃሚ መመሪያዎቹም ተካተዋል፣ ምርመራውን ከማድረግዎ በፊት እነሱን በጥንቃቄ ማንበብ አለብዎት። በድረ-ገጹ ላይም የመመሪያ ቪዲዮ አለን።

4.

የመመርመሪያው ኪቱ እንደ እስክሪብቶ የሚመስል ሲሆን ከጣትዎ ጫፍ ላይ የደም ጠብታ በመሰብሰብ እና በመምጠጥ ይሠራል፣ ከዚያም ለ15 ደቂቃዎች ይጠብቃሉ።

5.

በመመርመሪያው ኪት መስኮት ውስጥ የመስመሩን አቀማመጥ በመመልከት ውጤቱን ያገኛሉ። የተጠቃሚ መመሪያውን በጥንቃቄ ማንበብዎን ያስታውሱ!

6.

ማንኛቸውም ጥያቄዎች ካሉዎት ወይም ምርመራውን ብቻዎን ማድረግ ካልፈለጉ፣ ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ለአንዱ ስልክ መደወል ይችላሉ። እርስዎን ከሚረዱበት መንገዶች አንዱ ምርመራውን በሚያደርጉበት ጊዜ በሌላኛው የስልኩ ጫፍ ላይ በመሆን ነው።

የምርመራው ውጤት ፖዘቲቭ ከሆነ ምን ማድረግ አለብኝ?

በአሁኑ ወቅት ኤች.አይ.ቪ ጥሩ መድሃኒት ያለው በሽታ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይህ መድሃኒት ነፃ ነው፣ እናም በኖርዌይ ውስጥ ማንኛውም የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መድሃኒት የሚያስፈልገው ሰው ከፈለገ ሊወስድ ይችላል። በቀሪው ህይወትዎ መድሃኒቱን በየቀኑ መውሰድ ይኖርብዎታል፣ ነገር ግን ይህ ማለት እርስዎ አይታመሙም እናም ሌሎችን ሊበክሉ አይችሉም ማለት ነው። ኤች.አይ.ቪ ካለብዎ ነገር ግን መድሃኒትዎን ሚወስዱ ከሆነ፣ ሙሉ ለሙሉ መደበኛ የኖነ ህይወትን መኖር ይችላሉ – ከፈለጉ በተለመደው መንገድ ልጆች እንኳን መውለድ ይችላሉ። እዚህ ጋር ስለ ኤች.አይ.ቪ የበለጠ ማንበብ ይችላሉ። 

ምርመራው ፖዘቲቭ ከሆነ፣ የኤች.አይ.ቪ ፀረ እንግዳ አካላት ሊኖርዎት ይችላል ማለት ነው፣ እናም ውጤቱን ለማረጋገጥ እንደ ዶክተርዎ ካሉ የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ መጠየቅ አለብዎት። ከታች ካሉት ድርጅቶች ውስጥ አንዱን እንዲያነጋግሩ እንመክርዎታለን፣ ከዚያም እኛ በዚህ ላይ ልንረዳዎ እንችላለን። እኛን ማግኘት ካልፈለጉ፣ ጠቅላላ ሐኪምዎን እንዲያነጋግሩ እንመክርዎታለን።

ለአንዳንድ ሰዎች፣ በራስ መመርመሪያው በኤች.አይ.ቪ መያዛቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ብቻዎን እንዳልሆኑ እና እኛ ልንረዳዎ እንደምንችል ያስታውሱ። 

ምርመራው ሁልጊዜ ትክክለኛ የሆነ ውጤት እንደማይሰጥ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ለኤች.አይ.ቪ ከተጋለጡ ከ12 ሳምንታት በታች ከሆነ ምናልባት የምርመራው ውጤት ኔጌቲቭ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን አሁንም ኤች.አይ.ቪ ሊኖርብዎት ይችላል። ምርመራው ኤች.አይ.ቪ እንዳለቦት ካሳየ ይህ ትክክለኛ ውጤት ላይሆንም ይችላል። ስለዚህ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ እንዳለቦት ለማረጋገጥ የህክምና ባለሙያዎችን እርዳታ መጠየቅ እና የደም ምርመራ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። 

ማን ሊረዳኝ ይችላል?

Hivtest.no የአራት ድርጅቶች የትብብር ጥምረት ነው። እነዚህ ድርጅቶች ስለ ምርመራው ለሚኖርዎት ማንኛውም ጥያቄ ሊረዱዎት ይችላሉ፣ እናም ምርመራውን በሚያደርጉበት ጊዜ በቻት ወይም በስልክ ከእርስዎ ጋር ሊሆኑ ይችላሉ። የምርመራው ውጤት ፖዘቲቨ ከሆነም ሊረዱዎት ይችላሉ።

Church City Mission

በመላው ኖርዌይ በሚገኙ ከተሞች የሚሰራ ድርጅት ነው። በኤች.አይ.ቪ ዙሪያ ከ30 ዓመታት በላይ ስንሰራ ቆይተናል። በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎችን፣ ወይም ኤች.አይ.ቪ ያለበት ሰው ጋር ጓደኛ ወይም ዘመድ የሆኑ ሰዎችን መርዳት እንችላለን። ምርመራውን በሚያደርጉበት ጊዜ ስለራስ መመርመሪያው የሚኖርዎት ጥያቄዎችን ልንረዳዎት እንችላለን ወይም በስልክ ከእርስዎ ጋር መሆን እንችላለን። ሁሉም የኤች.አይ.ቪ አገልግሎቶቻችን እነሆ፦
 • ፈጣን የኤች.አይ.ቪ ምርመራ – ነፃ፣ ስምን የማያጋልጥ እና ውጤቱ በአንድ ደቂቃ ውስጥ።  
 • ስለ ኤች.አይ.ቪ መረጃ፣ ምክር እና መመሪያ። 
 • ከኤች.አይ.ቪ ጋር ለሚኖሩ ስደተኞች፣ ጎልማሶች እና ልጆች ትምህርትዎች።
 • ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችን የማግኘት እድል።
 • ከኤች.አይ.ቪ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ማረፊያ።

  
አድራሻ፦ Hammersborg Torg 3, NO-0179 Oslo.
ስልክ፦ +47 23 12 18 20
ስልክ፦ firmapost.aksept@bymisjon.no

አስተርጓሚ ከፈለጉ፣ የስልክ አስተርጓሚ በማዘጋጀት እንድንረዳዎት አስተርጓሚ እንደሚፈልጉ የሚነግረንን ሰው እንዲፈልጉ እና እንዲያስደውሉ እንመክራለን። 

 • ፈጣን የኤች.አይ.ቪ ምርመራ – ነፃ፣ ስምን የማያጋልጥ እና ውጤቱ በአንድ ደቂቃ ውስጥ።  
 • ስለ ኤች.አይ.ቪ መረጃ፣ ምክር እና መመሪያ። 
 • ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችን የማግኘት እድል።


አድራሻ፦ Bergljots gate 4 B, 7030 Trondheim
ስልክ፦ +47 47 47 33 05
ስልክ፦ health@bymisjon.no

 

አስተርጓሚ ከፈለጉ፣ የስልክ አስተርጓሚ በማዘጋጀት እንድንረዳዎት አስተርጓሚ እንደሚፈልጉ የሚነግረንን ሰው እንዲፈልጉ እና እንዲያስደውሉ እንመክራለን። 

 • ፈጣን የኤች.አይ.ቪ ምርመራ – ነፃ፣ ስምን የማያጋልጥ እና ውጤቱ በአንድ ደቂቃ ውስጥ።  
 • ስለ ኤች.አይ.ቪ መረጃ፣ ምክር እና መመሪያ።
 • ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችን የማግኘት እድል።


አድራሻ፦ Kong Oscars gate 62
ስልክ፦ +47 971 11 876

ኢሜል፦ bergen@minuttest.no

አስተርጓሚ ከፈለጉ፣ የስልክ አስተርጓሚ በማዘጋጄት እንድንረዳዎት አስተርጓሚ እንደሚፈልጉ የሚነግረንን ሰው እንዲፈልጉ እና እንዲያስደውሉ እንመክራለን። 

Helseutvalget ፋውንዴሽን

መቀመጫው ኦስሎ ውስጥ ነው፣ ነገር ግን በሌሎች የኖርዌይ ክፍሎችም እንገኛለን። ከ1983 ጀምሮ በኤች.አይ.ቪ ዙሪያ ስንሰራ ቆይተናል። ስለራስ-መመርመሪያው ማንኛውም አይነት ጥያቄ ካሎት ወይም የሆነ ሰውን ማናገር ከፈለጉ ልንረዳዎ እንችላለን። sjekkpunkt የሚባል ልዩ የምክክር እና ምርመራ አገልግሎትም አለን። ነፃ እና ሙሉ በሙሉ ስምዎን የማያጋልጥ ነው። ለታለመው ቡድን አባል የሆኑ የሰለጠኑ ሰራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች አሉን።
 • የምክክር እና ምርመራ አገልግሎት።
 • ውጤት በአንድ ደቂቃ ውስጥ የሚሰጥበት፣ ነፃ እና ስምን የማያጋልጥ ፈጣን የኤች.አይ.ቪ እና የቂጥኝ ምርመራ።
 •  ስለ ኤች.አ.ቪ እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች መረጃ እና መመሪያዎች። በቡና ቤቶች፣ በሳውናዎች እና በማሽከርከሪያ አካባቢዎችም ሊመለከቱን ይችላሉ። አድራሻ፦
Arbeidersamfunnets plass 1 (entrance via Torggata). ስልክ፦ +47 23 35 72 01 ስምን የማያጋልጥ ቻት፥ www.helseutvalget.no/sjekkpunkt
 • በአከባቢዎ ምርመራ መች እንደምንጀምር ማየት ይችላሉ፦ www.helseutvalget.no/sjekkpunkt
 • በBergen ውስጥ መደበኛ ምርመራዎችን እናደርጋለን – ስምን የማያጋልጥ እና ነፃ። በተጨማሪም Trondheimን፣ Stavangerን እና Kristiansandን እንጎበኛለን።

HivNorge

ከኤች.አይ.ቪ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች ለታካሚዎች እና ለመብቶቻቸው ብቸኛው የሃገሪቱ ድርጅት ነው። በኤች.አይ.ቪ ከተጠቁ ሰዎች ጋር፣ ራሳቸው ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ወይም ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖር ዘመድ ያላቸው ቢሆኑም፣ PrEP የሚወስዱ፣ በኤች.አይ.ቪ የመያዝ ስጋት ያለባቸው ወይም በማንኛውም ሁኔታ በኤች.አይ.ቪ የተጠቁ ሰዎችን መብትና ጥቅም ጠብቀን እንሰራለን። በፖለቲካ ደረጃ፣ ስራችን ኖርዌይ ውስጥ PrEP እንድናገኝ ረድቶናል፣ አጠቃላይ የፍትሐ ብሔር ህግጋትን በማሻሻል ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጾታዊ ግንኙነት በማድረጋቸው እንዳይቀጡ እና ማንኛውም ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖር ሰው የህይወት ኢንሹራንስ እና የአቅም ማነስ ዋስትናን እንዲወስዱ አረጋግጧል።
 • ስልክ፦  +21 31 45 80
 • ድህረ ገጽ፦ www.Hivnorge.no
 • Rosenkrantz gate 4, 0159 Oslo

Skeiv Verden

ከአናሳ ቦታ ለመጡ የLHBTIQ+ ሰዎች የተቋቋመ ብሔራዊ ድርጅት ነው። እኛ ከየትኛውም ሀይማኖት ወይም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ያልተገናኘን ነፃ ድርጅት ነን፣ እናም ማንኛውም ሰው ብሄራቸው ወይም ሀይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን ጾታዊ ዝንባሌያቸውን፣ የፆታ ማንነታቸውን ወይም የፆታ አገላለፁን ያለ መድሎ እንዲገልጽ ለማድረግ እንሰራለን። ሥራችን እውን የሆነው በበጎ ፈቃደኞቻችን፣ በአባሎቻችን፣ በአጋሮቻችን እና በጸሐፊዎቻችን አማካይነት ነው። በጎ ፈቃደኞቻችን እና አባላቶቻችን በዘርም ሆነ በዘር ባልሆነ ከተለያዩ አናሳ መደብዎች የተወጣጡ ናቸው። ኢላማ ያደረግናቸው ቡድናችን ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ ስደተኛ ሰራተኞችን፣ ተማሪዎችን፣ እና በኖርዌይ ውስጥ የተወለዱ አናሳ ዳራ ያላቸውን ያካትታል። Skeiv Verden የስደተኛ ዳራ ያላቸው ልዩ ሰዎች በግልጽ ራሳቸውን የሚሆኑበት፣ ተመሳሳይ ተሞክሮ ያላቸውን ሌሎችን የሚያገኙበት፣ ከአናሳ መደብ መምጣትና ልዩ መሆን ቀላል እንዲሆንላቸው ድጋፍ እና እውቀት የሚያገኙበት መልካም እና ደህንነቱ የተጠበቀ መድረክ ማመቻቸት ላይ ያተኩራል።

ስለ ኤች.አይ.ቪ መረጃ፦

ኤች.አይ.ቪ ምንድን ነው?

ኤች.አይ.ቪ የሰው ልጅ የበሽታ መከላከያ አቅም የሚቀንስ ቫይረስ (HIV, Human Immunodeficiency Virus) የሚል ትንታኔ ያለው ነው። ከሌላ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸም፣ እናቶች ወደ ሕጻናት ሊያስተላልፉት የሚችሉት ወይም በበሽታው በተያዘ ሰው ደም ምክንያት ሊያዙ የሚችሉበት በሽታ ነው። በኖርዌይ ውስጥ በኤች.አይ.ቪ የተያዘ ማንኛውም ሰው ነፃ መድሃኒት ይቀበላል። መድሃኒቱን ከወሰዱ ጤናማ ይሆናሉ እናም መደበኛ ህይወት መኖር ይችላሉ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሰዎች ኤች.አይ.ቪን አያስተላልፉም። ጥገኝነት ጠያቂ ከሆኑ ኤች.አይ.ቪ ቢኖርብዎትም ባይኖርብዎትም ማመልከቻዎ ላይ ተጽእኖ አያደርስም። ኤች.አይ.ቪ እና ኤድስ አንድ አይነት አይደሉም። በኤች.አይ.ቪ ከተያዙ፣ መድሃኒት እስካገኙ ድረስ መደበኛ ህይወት መኖር ይችላሉ። ኤድስ ማለት ኤች.አይ.ቪ ካለብዎት እና መድሃኒቱን የማይወስዱ ከሆነ ሊያዳብሩት የሚችሉት በሽታ ነው። መድሃኒት ካልወሰዱ በኤድስ ምክንያት ይሞታሉ።

ኤች.አይ.ቪ እንዴት ይተላለፋል?

 • ኤች.አይ.ቪ ካለበት ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከፈጸሙ እና ኮንዶም ካልተጠቀሙ በኤች.አይ.ቪ ሊያዙ ይችላሉ።
 • ኤች.አይ.ቪ ካለበት ሰው ጋር ተመሳሳይ መርፌን ከተጠቀሙ በኤች.አይ.ቪ ሊያዙ ይችላሉ።
 • ነፍሰ ጡር እናት ኤች.አይ.ቪ ካለባት እና በየቀኑ የኤች.አይ.ቪ መድሃኒት ካልወሰደች ህፃኑ በኤች.አይ.ቪ ሊያዝ ይችላል።
 • በአንዳንድ አገሮች የሌላ ሰው ደም በመውሰድ መክንያት (በኖርዌይ ግን አይደለም)።
 •  

ኤች.አይ.ቪ እንዴት አይተላለፍም?

 • በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎች በየቀኑ መድሃኒቶቻቸውን ከወሰዱ እና መድሃኒቱ በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ከሆነ፣ ኤች.አይ.ቪን አያስተላልፉም። 
 • በምራቅ፣ በእንባ ወይም በሽንት ኤች.አይቪ አይተላለፍብዎትም።
 • ከሆነ ሰው ጋር ግዜን በማሳለፍ ወይም ከጎረቤቶች፣ ጓደኞች ወይም ቤተሰብ ጋር በሚደረግ የለት ተእለት ግንኙነት ኤች.አይ.ቪ አይዝዎትም። 
 • ምግብ፣ መጠጥ፣ መጸዳጃ ቤት ወይም ሻወር ከተጋሩ ኤች.አይ.ቪ አይዞትም። 
 • ሌሎች ሰዎችን ቢስሙ ወይም ቢነኩ ኤች.አይ.ቪ አይዞትም።
 • ከእንስሳት ኤች.አይ.ቪ አይዞትም፣ ለምሳሌ፡ ትንኞች።
 • PrEP በኤች.አይ.ቪ እንዳይያዙ የሚከላከል መድሃኒት ነው። ከፍተኛ ተጋላጭነት የነበረው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ካደረጉ ይህንን መድሃኒት ከሐኪምዎ ማግኘት ይችላሉ። ማንኛውም አይነት ጥያቄ ካሎት እባክዎ ያናግሩን።

የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

 • ኤች.አይ.ቪ ብዙ ጊዜ ምንም አይነት ምልክት የለውም። 
 • ኤች.አይ.ቪ እንዳለብዎት ማወቅ የሚችሉት የደም ምርመራ በማድረግ ብቻ ነው።
  • ከጠቅላላ ሐኪምዎ ወይም በምርመራ ክሊኒክዎ የኤች.አይ.ቪ የደም ምርመራ ማድረግ ይችላሉ። ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ውጤቱን ይቀበላሉ።
  • በተለያዩ ቦታዎች ፈጣን የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግ ይችላሉ። ነጻ፣ ስምን የማያጋልጥ እና ወዲያውኑ ውጤቱን የሚያውቁበት ነው። 
  • እዚጋ ባለው ቻት በፖስታ ቤት በራስ የሚደረግ መመርመሪያን ማግኘት ይችላሉ።

 

ከኤች.አይ.ቪ ጋር መኖር ምን ይመስላል?

 • በአሁኑ ጊዜ ኤች.አይ.ቪ በሕይወት ዘመንዎ ሁሉ አብረው የሚኖሩት ሁኔታ ነው እንለዋለን። 
 • ቫይረሱን ለማስወገድ ምንም አይነት መድሃኒት ወይም መንገድ የለም፣ ነገር ግን ጥሩ መድሃኒት አንዳይታመሙ ወይም እንዳይሞቱ ያደርጋል።
 • በኖርዌይ ውስጥ ኤች.አይ.ቪ ያለበት ማንኛውም ሰው ነፃ መድኃኒት ያገኛል።
 • በቀሪው ዘመኖ መድሃኒቱን በየቀኑ መውሰድ ይኖርብዎታል።
 • መድሃኒቱን ከወሰዱ እና መድሃኒቱ በጥሩ ሁኔታ ከሰራ፣ ሌሎችን መበከል አይችሉም።
 • መድሃኒቱን ከወሰዱ እና መድሃኒቱ በጥሩ ሁኔታ ከሰራ፣ የፍቅር አጋሮን ወይም ህፃኑን ሳይበክሉ በተለመደው መንገድ ልጅ መፀነስ ይችላሉ።
 • ይህ ማለት ኤች.አይ.ቪ እንደሌለበት ሰው ረጅም እና ጤናማ ህይወት ሊኖርዎት ይችላል ማለት ነው። የወንድ ጓደኞች/የሴት ጓደኞች እንዲሁም ልጆች ሊኖርዎት ይችላል፣ ስራ ኖርዎት መደበኛ እና ጤናማ ህይወት መኖር ይችላሉ።
 • በኖርዌይ ወደ 4,000 የሚጠጉ በኤች.አይ.ቪ የተያዙ ሰዎች አሉ። በሌላ አነጋገር ኤች.አይ.ቪ ካለቦት ብቻዎን አይደሉም ማለት ነው። ማንኛውም አይነት ሰው በኤች.አይ.ቪ ሊያዝ ይችላል፣ ወንድ ወይም ሴት ቢሆኑም፣ የመጡበት ሀገር ከየትም ይሁን ወይም ወሲብ አብረውት የፈጸሙት ሰው ምንም ለውጥ አያመጣም።
 • በርካታ ድርጅቶች በመላ ሃገሪቱ በኤች.አይ.ቪ ለተያዙ ሰዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። ጥሩ መድኃኒት እያለም እንኳ ከኤች.አይ.ቪ ጋር መኖር ለሁሉም ሰው ቀላል እንዳልሆነ እናውቃለን።

በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ሌሎች ኢንፌክሽኖች፦

እንደ ቂጥኝ፣ ጨብጥ እና ክላሚዲያ ያሉ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖችንም እንዲመረመሩ እንመክራለን። ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ፣ አዲስ የፍቅር አጋር ሲዪዙ ወይም የወሲብ አሻንጉሊቶችን ከተጋሩ በኋላ ምርመራ ማድረግ ይኖርብዎታል። በበሽታው ቢያዙም እንኳን ሁሉም ሰው ምልክቶችን አያሳይም። ሌላ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ካሉብዎት ከፍተኛ የሆነ በኤች.አይ.ቪ የመያዝ አደጋ ውስጥ ነዎት።

ጠቅላላ ሃኪምዎ ሁሉንም በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ሊመረምርዎት ይችላል፣ ወይም በመመርመሪያ ክሊኒክ ውስጥ ሊመረመሩ ይችላሉ (አገናኝ፦ test clinic.

Ta kontakt med
oss her

Helseutvalget – Arbeidersamfunnets plass 1, 0181 Oslo. Org. nr. 916 551 665.

Samarbeidspartnere

Design: Bielke&Yang | Design & utvikling: Marialyn Andreassen GFX

© Copyright Helseutvalget 2022 | Privacy and cookies